Ezekiel 34

እረኞችና በጎች

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ራሳቸውን ብቻ ለሚንከባከቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች መንጋውን ማሰማራት አልነበረባቸውምን? 3ጮማውን ትበላላችሁ፤ ከጠጕሩ የተሠራውን ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውን ዐረዳችሁ፤ ነገር ግን መንጋውን አትንከባከቡትም። 4ደካማውን አላበረታችሁትም፤ በሽተኛውን አልፈወሳችሁትም፤ የተጐዳውንም አልጠገናችሁትም። የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትንም አልፈለጋችሁም፤ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው። 5ስለዚህ እረኛ የለምና ተበተኑ፤ በመበተናቸውም ለአራዊቱ ሁሉ መብል ሆኑ። 6በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኰረብታው ላይ ተንከራተቱ። በምድር ሁሉ ተበተኑ፤ የፈለጋቸውም፤ የፈቀዳቸውም የለም።

7“ ‘ስለዚህ እናንት እረኞች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 8በሕያውነቴ እምላለሁ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኞቼ መንጋዬን ስላልፈለጉ፣ ከመንጋዬም ይልቅ ራሳቸውን ስለ ተንከባከቡ፣ መንጋዬ እረኛ ዐጥቶ ለንጥቂያ ተዳርጓል፤ ለአራዊትም ሁሉ መብል ሆኗል። 9ስለዚህ እረኞች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም።

11“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም። 12እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። 13ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ። 14በመልካሙ ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤ የእስራኤል ተራሮች ከፍታም የግጦሽ መሬት ይሆናቸዋል። በመልካሙ ግጦሽ መሬት ላይ ይተኛሉ፤ እዚያም በእስራኤል ተራሮች ለምለም መስክ ላይ ይመገባሉ። 15እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም። ይላል ጌታ እግዚአብሔር 16የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።

17“ ‘መንጋዬ ስለ ሆናችሁት ስለ እናንተ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በበግና በበግ መካከል፣ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ። 18በለምለሙ መስክ ላይ መመገቡ አይበቃችሁምን? የተረፈውን መሰማሪያችሁን ደግሞ በእግራችሁ መረጋገጥ ይገባችኋልን? ንጹሕ ውሃ መጠጣቱ አይበቃችሁምን? የተረፈውንስ በእግራችሁ ማደፍረስ ይገባችኋልን? 19መንጋዬ የረጋገጣችሁትን መመገብና በእግራችሁ ያደፈረሳችሁትን መጠጣት ይገባዋልን?

20“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፤ “እነሆ እኔ ራሴ በሰባው በግና በከሳው በግ መካከል እፈርዳለሁ። 21ደካሞቹን በጎች በጐናችሁና በትከሻችሁ ስለምትገፈትሩ፣ እስኪባረሩም ድረስ በቀንዳችሁ ስለምትወጓቸው፣ 22እኔ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ለንጥቂያ አይዳረጉም፤ በአንዱ በግና በሌላውም በግ መካከል እፈርዳለሁ። 23በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ፣ ባሪያዬን ዳዊትን አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እረኛቸውም ይሆናል። 24እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እሆናለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው ገዥ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”

25“ ‘ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚያም ምድሪቱን ከዱር አራዊት ነጻ አደርጋለሁ፤ እነርሱም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በደንም ውስጥ በሰላም ይተኛሉ። 26እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካለሁ።
ወይም እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ
በወቅቱም ዝናብ አወርድላቸዋለሁ፤ ዝናቡም የበረከት ዝናብ ይሆናል።
27የየሜዳው ዛፍ ፍሬ ይሰጣል፤ መሬቱም እህል ያበቅላል። ሕዝቡም በምድሪቱ ላይ በሰላም ይኖራሉ። የቀንበሮቻቸውን ማነቆ ሰብሬ በባርነት ከገዟቸው እጅ ሳድናቸው፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 28ከእንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ንጥቂያ አይዳረጉም፤ የዱር አራዊት አይቦጫጭቋቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም። 29ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ የራብ ተጠቂ እንዳይሆኑ፣ የአሕዛብንም ስድብ እንዳይሸከሙ ፍሬ በመስጠት የታወቀውን መሬት እሰጣቸዋለሁ። 30ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንደ ሆንሁ፤ የእስራኤል ቤት የሆኑት እነርሱም ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር 31እናንተ በጎቼ የማሰማሪያዬ በጎች ያልኋችሁ፣ ሕዝብ ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

Copyright information for AmhNASV